ለፈተናዎች ያልተንበረከከው ፋብሪካ
**************
ሕዳር 01/2015 ዓ.ም ባሕር ዳር፤
በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪና ተመራጭ የፕላስቲክ ፋብሪካ ሆኖ የመገኘት ዓላማን ሰንቆ በመንቀሳቀስ በርካታ አመርቂ ውጤቶችን ያስመዘገበው የአማራ ፓይፕ ፋብሪካ በበርካታ ፈተናዎች ታጅቦ ባለፈው የ2014 በጀት ዓመት 189,376,423.00 ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡
ለዚህ ውጤት መገኘትም ሰራተኞች፣ የማኔጅመንት አባላትና የቦርድ አመራሮች ተቀናጅተውና ተናበው ከመስራት ባለፈ የፋብሪካውን ምርቶች ከክልሉ ውጭ በአፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ፣ አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ኢትዮ ሶማሊያና ሌሎች ክልሎች ድረስ ገብቶ በመሸጥ ተደራሽነትን ለማስፋት የተደረገው እንቅስቃሴ ተጨባጭ ውጤት እንዳስገኘ ተመላክቷል፡፡
ፋብሪካው በክልላችን ውስጥ ካሉት የመንግስት የልማት ድርጅቶች በተለየ ሁኔታ ተከታታይነት ያለው የትርፍ እድገት በማስመዝገቡ ከልማት ድርጅቶች አስተዳደር የዋንጫና የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
በተመሳሳይም በበጀት ዓመቱ 88,082,574.68 ብር ግብር በመክፈል በፌደራል ደረጃ የዓመቱ ምርጥ ግብር ከፋይ በመሆን በክብርት ፕሬዘዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የዋንጫ ሽልማትን ተቀብሏል፡፡
ምን ይሄ ብቻ!!
በ2014 በጀት ዓመት በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፎች ላይ ፈጥኖ ደረሽ በመሆን በገንዘብ ብቻ 25,543,653.06 ብር በላይ በመለገስ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፤ አጋርነቱንም አሳይቷል፡፡
በተያዘው የ2015 በጀት ዓመትም 10 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምርት በማምረትና 1 ነጥብ 59 ቢሊዬን ብር ሽያጭ በማከናወን ከ265 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ለማግኘት ታቅዶ በመትጋት ላይ የሚገኝ መሆኑን የፋብሪካው ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ ወርቁ ባዬ አስረድተዋል፡፡
በም/ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪና የፋብሪካው የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ሰማ ጥሩነህ (ዶ.ር) በበኩላቸው ፋብሪካው ወደፊትም የበለጠ ትርፋማ እንደሚሆን ሙሉ እምነት ያላቸው መሆኑን በመግለጽ የቦርድ አባላትም ስትራቴጂክ የሆኑ የትኩረት ነጥቦችን ለይተው ወደ ተግባር የገቡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም ደግሞ ማሽኖች ዘመኑን የሚዋጁና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆኑ ለማስቻል የዕድሳትና የማስፋፊያ ስራዎች እንደሚተገበሩ ጠቁመዋል፡፡

የዶላር ችግርን ለመቅረፍም ምርቱን ከኢትዮጵያ ውጭ ወደሌሎች የአፍሪካ አገራት በመላክ ሙሉ በሙሉም ባይሆን በከፊል የምንዛሬ ዕጥረቱን ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያም የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው የካይዘን ልማት ቡድኖች፣ በስራቸውና በመልካም ስነ-ምግባራቸው አርዓያ መሆን ለሚችሉ ሰራተኞችና ፋብሪካው እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለነበራቸው የማኔጅመንት አባላትና የቀድሞ የቦርድ አባላት የገንዘብ፣ የአይነትና የዕውቅና ሰርትፊኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ተሸላሚ የሆኑት ሠራተኞችም የማበረታቻ ሽልማቱ ተነሳሽነታቸውን እንደጨመረላቸውና ለበለጠ ውጤት የማትጋት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
መልካም የስራ ጊዜ እንዲሆንላችሁ ምኞታችን ከልብ ነው!!